በየደረጃው የሚደረጉ የጸረ ሙስና ትግሎች ለችግሩ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ ዘርፎች ልዩ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ተጠቆመ። የክልሉ የፍትህ አካላት ማሰልጠኛና የህግ ምርምር ማዕከል የፍትህ ስርኣቱ መጠናከር ሙስናና ብልሹ አሰራርን በመዋጋት ረገድ በሚኖረው ሚና ዙሪያ ስልጠና ሰጥቷል።
በየደረጃው የሚደረጉ የጸረ ሙስና ትግሎች ለችግሩ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ ዘርፎች ልዩ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ተጠቆመ።
የክልሉ የፍትህ አካላት ማሰልጠኛና የህግ ምርምር ማዕከል የፍትህ ስርኣቱ መጠናከር ሙስናና ብልሹ አሰራርን በመዋጋት ረገድ በሚኖረው ሚና ዙሪያ ስልጠና ሰጥቷል።
(ወልቂጤ፣ ታህሳስ 24/2017) ፣ በየደረጃው የሚደረጉ ህዝባዊም ሆነ መንግስታዊና ተቋማዊ የጸረ ሙስና ትግሎች ለችግሩ ይበልጥ ተጋላጭ በሆኑ ዘርፎች ላይ ልዩ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው ተጠቁሟል።
የክልሉ የፍትህ አካላት ማሰልጠኛና የህግ ምርምር ማዕከል የፍትህ ስርኣቱ መጠናከር ሙስናና ብልሹ አሰራርን በመዋጋት ረገድ በሚኖረው ሚና ዙሪያ ለኮሚሽኑ ተጠሪ የሴክተር መስሪያ ቤት የስነ ምግባር ኦፊሰሮች ስልጠና ሰጥቷል።
የክልሉ የፍትህ አካላት ማሰልጠኛና የህግ ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሽተባህ አባድር በዚሁ ወቅት እንዳሉት እንደ ግዥ፣የጨረታና ሌሎች ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ ዘርፎችና አሰራሮች ልዩ ትኩረት ይሻሉ።ለዚህ ትልቁ መፍትሄ ግልጽና ተጠያቂነትን የተላበሰ አሰራር መዘርጋትና አገልጋዮች የላቀ ስነ ምግባርን እንዲላበሱ ማድረግ እንደሆነም ገልጸዋል ።
የሙስና ወንጀል ውስብስብና ዘርፈ ብዙ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሙሽተባህ ይህን ሊመጥን የሚችል ቅንጅታዊ የመከላከል ስራና ይህን በአግባቡ የሚያግዝ የፍትህ ስርኣት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል ። የክልሉ ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ማሞ ቴጋ በበኩላቸው ሙስናን የመቅረፍ ጥረቶች ለተጋላጭ ዘርፎችና አሰራሮች የተለየ ትኩረት መስጠትን ይጠይቃል ።
ብልሹ አሰራርንም ሆነ ሙስናን ለመከላከል ለችግሩ በር የሚከፍቱ አሰራሮችና አደረጃጀቶችን ከመከታተል ባሻገር በጠንካራ የፍትህ ስርኣት ታግዞ ህግን በአግባቡ መረዳትና በቁርጠኝነት መተግበር ይገባል ሲሉ ኮሚሽነር ማሞ ጠቁመዋል።ጠንካራ የፍትህ ስርኣትና የዳበረ ቅንጅታዊ አሰራር የተደራጀ የሙስና ወንጀልን ለመከላከል እንደሚያስችልም ተናግረዋል ።
ሙስናን ለመዋጋት ክልላዊ ግብረ ሃይል ተቋቁመ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የገለጹት አቶ ማሞ በክልሉ በተደረገ የተቀናጀ ጥረት ሊመዘበር የነበረ በርካታ ገንዘብ ማዳን ተችሏል ብለዋል።የማዕከሉ ምክትል ዳይሬክተር ወ/ሮ በቱላ አብደላ እንዳሉት ደግሞ የክልሉ የፍትህ አካላት ማሰልጠኛና የህግ ምርምር ማዕከል የፍትህ ዘርፉን አቅም በማጎልበት በተለይም የህግ አካላት ብቁ ሆነው የተሻለ ህዝባዊ አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ በኩል ሚናውን እየተወጣ ይገኛል።
የህግ ባለሙያ የሆኑትና ስልጠናውን የሰጡት አቶ በረከት ከድር የህግ ግንዛቤና አተገባበርን ማጎልበት ሙስናን ለመታገል ቁልፍ ሚና አለው ብለዋል። ሙስናን ለመቅረፍ እንደ ሀገር የህግ፣የአሰራርና የፖሊሲ ማዕቀፎች መዘርጋታቸውን ያብራሩት የህግ ባለሙያው ጸረ ሙስና ትግሉን በተደራጀ መንገድ ማስተባበርና ማቀናጀት እንደሚገባ አስረድተዋል ።
የፍትህ ስርኣቱ መጠናከር ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም አቶ በረከት ተናግረዋል ። ይህን በሚመለከት የወጡ ህጎችን በአግባቡ ተግባር ላይ ማዋል ችግሩን በመከላከል ረገድ የማይተካ ሚና እንዳለውም ጠቁመዋል ።በስልጠናው የክልሉ የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኦፊሰሮች ፣በክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተወካዮች፣ የክልሉ የፍትህ አካላት ማሰልጠኛና የህግ ምርምር ማዕከል አመራሮችና የሴክተር መስሪያ ቤቶች የስነ ምግባር ኦፊሰሮች ተሳትፈዋል።