የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ በስነ- ምግባርና ፀረ-ሙስና ዳይሬክቶሬት ለዞን ጤና መምሪያዎች፣ለልዩ ወረዳ ጤና ጽ/ቤቶችና ለኮሌጅ ለስነ - ምግባርና ፀረ- ሙስና ቡድን መሪዎች የአሰልጣኞች ስልጠና በሀላባ ዞን ቁሊቶ ከተማ እየተሰጠ ይገኛል
ጥር 19/2017 ዓ/ም
ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል ሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለፀ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ በስነ- ምግባርና ፀረ-ሙስና ዳይሬክቶሬት ለዞን ጤና መምሪያዎች፣ለልዩ ወረዳ ጤና ጽ/ቤቶችና ለኮሌጅ ለስነ - ምግባርና ፀረ- ሙስና ቡድን መሪዎች የአሰልጣኞች ስልጠና በሀላባ ዞን ቁሊቶ ከተማ እየተሰጠ ይገኛል
የማዕ/ኢት/ክልል የስነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ምክትል ኮምሽነርና የት/ት ስልጠና እና አዉታሮች ማስተባበሪያ ዘርፍ ሀላፊ ወ/ሮ ታየች ሞላ የእለቱን ፕሮግራም ባስጀመሩበት ወቅት ላይ እንደተናገሩት የሀብት ማሳወቅና ማስመዝገብ ሙስናንና ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከል እና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል ።
በሀገራችን ብሎም በክልሉ ብልሹ አሰራር ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎችን እያሳያ ቢሆንም ዉጤታማነቱን ይበልጥ ለማስቀጠል ይህ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ትልቅ አቅም አለዉ ያሉት ወ/ሮ ታየች ብልሹ አሰራርን ለመከላከል በተቋማችሁ ብቻ ሳትገደቡ ወደታችኛዉ መዋቅር በመዉረድ የህብረተሰቡን የግንዛቤ ክፍተት ማሳደግ እንደሚገባ አስረድተዋል ።
ተቋማት ከብልሹ አሰራር የፀዱ እንዲሆን ችግሩ ከመፈጠሩ በፊት መከላከል ላይ በትኩረት መሥራት ይገባል ያሉት ምክትል ኮምሸነሯ የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ዉስንነቶችን ለመቅረፍ በልዩ ትኩረት መስራት ተጠባቂ ስለመሆኑም አስገንዝበዋል ።
የማዕ/ኢት/ክልል የጤና ቢሮ የስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ኤልሳቤጥ በጋሻዉ በበኩላቸዉ ሙስናና ብልሹ አሰራር የሀገራችንን ብሎም የክልላችንን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገት ከመግታቱም ባሻገር የልማት፣ የዲሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ግንባታን የሚያደናቅፍ ተግባር ነዉ ብለዋል።
እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ ክልሉ የፀረ-ሙስና ትግሉን ይበልጥ በማጠናከር የተጀመረውን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገትና ልማትን ለማስቀጠል በርካታ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ አክለዋል ።
በጤናው ሴክተር የትራንስፎርሜሽን እቅድ ለማሳካት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወን ህብረተሰቡ ጥራት ያለዉን የጤና አገልግሎት በላቀ ደረጃ ተደራሽ እያደረገ እና ዉጤት እያመጣ ይገኛል ያሉት ዳይሬክተሯ እየመጣ ያለዉን ዉጤት በሙስናና ብልሹ አሰራር እንዳይደናቀፍ የፀረ-ሙስና ትግሉን በማጠናከር የመንግስት እና የህዝብ ሀብት ለታለመለት ዓላማ እንዲዉል የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በትኩረት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል
እየተሰጠ የሚገኘዉ የአሰልጣኞች ስልጠና የተለያዩ ሰነዶች እየቀረበ ሲሆን ስልጠናዉ ለ3 ተከታታይ ቀናት እንደሚቀጥል ለማወቅ ተችሏል