Skip to main content

የክልሉ ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን የስነ ምግባር አውታሮች የትብብርና ቅንጅት ፎረም በአዲስ መልክ ተቋቋመ።

የክልሉ ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን የስነ ምግባር አውታሮች የትብብርና ቅንጅት ፎረም በአዲስ መልክ ተቋቋመ።

ኮሚሽኑ የሁሉንም የመንግስት ተሿሚዎች 

ሀብት ማሳወቅና ምዝገባ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።

ጥቅምት 23/2017 የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን የስነ ምግባር አውታሮች የትብብርና ቅንጅት ፎረም በአዲስ መልክ በወራቤ ከተማ ተቋቁሟል።

ፎረሙ የሴክተሮችና ተቋማት የስነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች የጋራ መድረክና ቅንጅታዊ አሰራር የሚያጎለብት ሲሆን በክላስተር ደረጃ ብሎም ክልል አቀፍ በሆነ መልኩ የጸረ ሙስና ትግልን ለመምራትና ስነ ምግባርን ለማጎልበት የሚያግዝ ነው።ይህ ክልላዊ ፎረም ሙስናን ከመታገል ባሻገር በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍና ተሞክሮዎችን ለማስፋት እንደሚጠቅም የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነርና የትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ሃላፊ ወ/ሮ ታየች ሞላ አስታውቀዋል ።

በሌላ በኩል በክልሉ የዘንድሮውን አለም አቀፍ የጸረ ሙስና ቀን ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ባስተፈ መልኩ በንቅናቄ ለማክበር ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ወ/ሮ ታየች ተናግረዋል።በኣሉ በአለም አቀፍ ደረጃ ለ21ኛ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ20ኛ ጊዜ በተለያዩ ዝግጅቶች ታስቦ የሚውል ሲሆን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በአዲስ መልክ ከተዋቀረ በሗላ ለ2ኛ ጊዜ ይከበራል።በዚሁ መሰረት በቀበሌና ትምህርት ቤት፣ በልዩ ወረዳና ዞን ደረጃ ከህዳር 10 እስከ 16 ባሉት ቀናት ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ከተከበረ በሗላ ህዳር 21/2017 ቡታጅራ ከተማ ላይ በሚካሄድ ክልል አቀፍ የማጠቃለያ ዝግጅት ይጠናቃል ብለዋል። በኣሉ በጸረ ሙስና ትግሉ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ግንዛቤና የህዝብ ንቅናቄ መፍጠር እንደሆነ ወ/ሮ ታየች ጠቁመዋል ።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም ኮሚሽኑ የሁሉንም የመንግስት ተሿሚዎች ሀብት ማሳወቅና ምዝገባ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነርና የሙስና መከላከል ዘርፍ ሃላፊ አቶ ፋሲካ ጌታቸው እንዳሉት በአዋጅ መሰረት የተሿሚ አመራሮች ሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ስራን የግለሰቦችን ሚስጥር በጠበቀ መልኩ በአዲስ መልክ በማስጀመር እስከ ቀጣዩ ህዳር ወር አጋማሽ ድረስ ለማጠናቀቅ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።

ምዝገባ ብቻ ሳይሆን ማጣራት እንደሚደረግ ያነሱት አቶ ፋሲካ አላማው ምንጩ ያልታወቀ ሀብት እንዳይኖር ማድረግና ዜጎች ሀብትን በላብና በጥረታቸው ብቻ የሚያፈሩበትን አስተሳሰብ ማስረጽ መሆኑን ጠቁመዋል።እስከ አሁን ባለው ሂደትም ሀብት ማስመዝ ያለባቸውን አመራሮች የመለየት፣ የሙስና ተጋላጭ ዘርፎችን የማጥናትና ለምዝገባ የሚረዳ ቅፆች ዝግጅት መጠናቀቁን አቶ ፋሲካ አብራርተዋል ።

በዚህ በጀት አመት የሁሉንም ተሿሚ አመራር ሀብት ምዝገባና ማሳወቅ ሂደት ለማጠናቀቅ ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል ።ኮሚሽኑ ለዚህ ያግዘው ዘንድ የዲጅታል ሲስተም ምዝገባና መረጃ አያያዝ ይዘረጋል ብለዋል።ሙስናን የመዋጋት ተግባር የአንድ ተቋም ስራና ሃላፊነት መሆን የለበትም ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ ትምህርት ቤቶችን መሰረት አድርጎ ታዳጊዎች ላይ መስራትና የተጠናከረ ማህበረሰብ አቀፍ የትግል ንቅናቄ ሊፈጠር እንደሚገባ ተናግረዋል ።

Image